ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጸጸሙን አስመልክቶ ዛሬ ጥር 28 ቀን 2018 ዓ.ም በዋና መ/ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከከፍተኛ የአክሲዮን ባለድርሻዎች ጋር የምክክር መርሃ-ግብር አካሂዷል፡፡
መርሃ-ግብሩን በንግግር የከፈቱት የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ስብሳቢ አቶ ሺሰማ ሸዋነካ ለተጋበዙ ባለድርሻ አካላት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን ባንኩ ቀደም ሲል ከነበረበት ሁኔታ ወጥቶ በሁሉም መለኪያዎች አበረታች ስኬት እያስመዘገበ እንደሚገኝ አሳውቀዋል፡፡
የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሄኖክ ከበደ በበኩላቸው ባንኩ አስተማማኝ መሰረት ላይ እንዲቆም የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ ነድፎ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመው በያዝነው በጀት ዓመትም በሁሉም ዋና ዋና መመዘኛዎች ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን እና ለዚህም ደንበኞች፣ ባለድርሻ አካላት፤ የቦርድ አባላትና የባንኩ ከፍተኛ አመራር አባላት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀራርበው በመስራት ላሳዩት ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበው ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ባንኩ በዲጂታል አገልግሎት እንዲሁም ደንበኛ ተኮር አገልግሎቶችን በመስጠት ረገድና ቅርንጫፎችን ለደንበኞች ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን በምክክር መድረኩ ላይ ተጠቁሟል፡፡ ከትርፋማነት አንፃርም በተገባደደው ግማሽ ዓመት ከታክስ በፊት የ2.2 ቢሊዮን ብር ትርፍ መመዝገቡ ተመልክቷል፡፡
ተሳታፊዎችም በበኩላቸው ባንኩ ከነበረበት ሁኔታ ወጥቶ እያስመዘገበ ያለው ስኬት የሚደነቅ መሆኑን የገለፁ ሲሆን በቀጣይ የባንኩን ዲሬክተሮች ቦርድ እና ከፍተኛ አመራሩን በቅርበት በማገዝ የተጀመረውን ስኬታማ ጉዞ እንደሚያስቀጥሉ ቃል በመግባት መርሃ-ግብሩ ተጠናቋል፡፡






