ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ከፕራይም ኦል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ጋር በመተባበር፣ በዘርፉ የመጀመሪያ የሆነውን ሁሉን-በአንድ የያዘ የዲጂታል ሥርዓት «ንብተራ-ደረሰኝ» በሚል ስያሜ፣ ዛሬ መስከረም 29 ቀን 2019 ዓ.ም. በባንኩ ዋና መ/ቤት በይፋ አስጀመረ።
የአገልግሎቱን በይፋ መጀመር አስመልክቶ፣ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባንኩ ሪቴይልና ኤስኤምኢ ባንኪንግ ቺፍ ኦፊሰር አቶ ሙሉቀን ደምሴ፤ በባንካችን የተደረገው ይህ አዲስ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ተነሳሽነት፣ ነጋዴዎች፤ በገቢዎች ሚኒስቴር ዕውቅና የተሰጠውን የፕራይም ኦል ትሬዲንግ የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ እና የድርጅት ሀብት አስተዳደር ሥርዓትን፤ ከባንኩ ጠንካራ የዲጂታል መሠረተ ልማት ጋር በማቀናጀት፣ በአንድ ነጻ ስማርት ፖስ አማካኝነት የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ እንዲያወጡ፣ የክፍያ እና የንግድ ሥርዓታቸውን እንዲያዘምኑ የሚያስችላቸው አስተማማኝ ቴክኖሎጂ መሆኑን አመልክተዋል።
አክለውም፤ አዲሱ የ«ንብተራ-ደረሰኝ» አገልግሎት፣ ጊዜ ያለፈባቸውንና እርስ በእርስ የማይገናኙ የሽያጭ መመዝገቢያ ካሽ ሬጂስተሮችን፤ በአንድ እጅ ብቻ በሚያዝ ዘመናዊ ስማርት ፖስ በመተካት፣ ነጋዴዎች ለደንበኞቻቸው የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት ያስችላቸዋል ብለዋል።
በሌላም በኩል፤ የፕራይም ኦል ትሬዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ውብሸት አዝመራው፣ አዲሱ ንበተራ-ደረሰኝ የክፍያ ሥርዓት አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፤ “ንብተራ-ደረሰኝ” ነጋዴዎች በርካታና የተነጣጠሉ መሣሪያዎችን በመጠቀም ሲሰጡ የነበረውን ኋላቀር አገልግሎት በማስቀረትና፣ በንግዱ ዘርፍ ሲስተዋሉ የነበሩትን የአሠራር ፈተናዎችን በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በንብተራ ዲጂታል የባንክ አገልግሎት ስር በርካታ መተግበሪያዎችን በማካተት፤ ለኅብረተሰቡ የክፍያ አማራጮችን በማቅረብ ከፍተኛ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ይታወቃል፡:









