Internet Banking
Internet Banking

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በአዲስ መልክ ሥራውን ወደ ማከናወን ተሸጋገረ!

የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ታህሣሥ 18 ቀን 2ዐ16 ዓ. ም. የባንኩን ባለአክሲዮኖች 24ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በብሔራዊ ባንክ አመቻችነትና ታዛቢነት ባደረገው ምርጫ የተመረጡት የቦርድ አባላት ዝርዝር ጥር 24 ቀን 2ዐ16 ዓ. ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፀድቋል፡፡ በዚህም መሠረት አዲሱ ቦርድ ባንኩን የማስተዳደር ተግባሩን ከጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ተረክቧል፡፡

አዲሱ ቦርድ ባንኩ ያለበትን ከፍተኛ ተግዳሮት በመገንዘብ ፈጥኖ ወደ ሥራ በመግባት የራሱን አመራር እና የንዑስ ኮሚቴዎችን ድልድል በማካሄድ አቶ ሺሰማ ሸዋነካን በሊቀመንበርነት እንዲሁም ዶ/ር ወንድሙ ተክሌን በምክትል ሊቀመንበርነት መርጧል፡፡ በቀጣይም ቦርዱ፣ ባንኩ ያለበት አሁናዊ ሁኔታ ጊዜ የማይሰጥና ቀን ከሌት መስራትን እንደሚጠይቅ ከግንዛቤ በማስገባት የባንኩን ስምና ዝና  ወደነበረበት መመለስን እንዲሁም የባንኩን ዘለቄታዊ ጥቅም ማስጠበቅን ዋነኛ ግቡ ያደረገውን የባንኩን የመልሶ ማደራጃ የዘጠና ቀናት ዕቅድ (90 days Turnaround Plan) ተልሟል፡፡

ቦርዱ ከባንኩ የማኔጅመንት አባላት እስከዋና ክፍል ኃላፊ ድረስ  ካሉት የሥራ ኃላፊዎችም ጋር ትውውቅና ውይይት አካሂዷል፡፡ ቦርዱ በተጨማሪም እንደ ባንክ እንዲሰሩ ባሰባቸው ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ በዚህም ቦርዱ የተለመውን የመልሶ ማደራጃ ዕቅድ ይፋ በማድረግ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በተረጋጋ መንፈስና በጥንቃቄ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ መመሪያ አስተላልፏል፡፡ የቦርዱ ንዑሳን ኰሚቴዎችም ጊዜ ሳይሰጡ ከባንኩ የማኔጅመንት አባላት ጋር በቀረቡ ሪፖርቶችና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አካሂደዋል፤ አቅጣጫም አስቀምጠዋል፡፡

አዲሱ ቦርድ የካቲት 6 ቀን 2ዐ16 ዓ. ም. ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ከክቡር አቶ ማሞ ምህረቱ፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ ከክቡር አቶ ሰሎሞን ደስታ እና ከሌሎች የባንኩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ትውውቅ አድርጓል፡፡

በስብሰባውም ክቡር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አዲሱ ቦርድ ከፊቱ የተደቀኑትን ተግዳሮቶች ግዙፍነት በአፅንዖት አስገንዝበው ሃላፊነቱን በልዩ ቁርጠኝነት እና በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት እና ፍጹም ታማኝነት እንዲወጣ በአፅንዖት አሳስበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአዲሱን ቦርድ የስራ አፈፃፀም በቅርበት እንደሚከታተልና እንደሚገመግም የባንኩ ገዢ በስብሰባው ላይ ጨምረው አስታውቀዋል፡፡

በዋነኛነት ክቡር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በባንክ ሴክተር ቀደምት እና ጠንካራ ከሆኑት ባንኮች መካከል የሚመደብ መሆኑን አስታውሰው በቀጣይም አዲሱ ቦርድ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ወደነበረበት ደረጃ በሚያደርገው ጉዞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከጐኑ በመሆን በቅርበት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚሰጠው የባንኩ ገዢ አረጋግጠዋል፡፡

አዲሱ ቦርድ፤ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ከፍተኛ ተግዳሮት በገጠመው በዚህ ወቅት ከጐኑ በመሆን ፈተናዎቹን በስኬት እንዲወጣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እያደረገለት ለቆየው እና ወደፊትም ለሚቀጥለው ሁሉ አቀፍ ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር ከፍተኛ አክብሮቱን እና ላቅ ያለ ምስጋናውን በባንኩ ማህበረሰብ ስም ማቅረብ ይወዳል፡፡

በዚህ አጋጣሚ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ባለፉት ጊዜያት በገጠመው ተግዳሮት በደንበኞቻችን፣ በአስቀማጮቻችን፣ በንግድ አጋሮቻችን፣ እንዲሁም በሌሎችም ባለድርሻ አካላት ላይ ለደረሰው መጉላላት የባንኩ ቦርድ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ በቀጣይም በምናደርገው ማስተካከያ ደንበኞቻችንን፣ አስቀማጮቻችንን፣ አጋሮቻችንን እና ባለድርሻ አካላትን በተሻሻለ አገልግሎት እንደሚክስ አዲሱ ቦርድ በመላ የባንኩ ሠራተኞች ስም ቃል ይገባል፡፡

አዲሱ ቦርድ ተከታታይነት ያለው የምክክር መድረኮች በማመቻቸት ከደንበኞቻችን፣ ከተበዳሪዎቻችን፣ ከባለአክሲዮኖች፣ ከስመጥር ነጋዴዎችና ከሌሎች የንግድ አጋሮቻችን፣በተጨማሪም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በተከታታይ ውይይት የሚያደርግ ሲሆን በእነዚህም መድረኰች የደንበኞቻችንን፣ የባለአክሲዮኖቻችንን፣ እና የባለድርሻ አካላትን ገንቢ አስተያየት በመቀበል የባንካችንን የአገልግሎት ጥራት ለማሻሻል በትጋት ይሠራል፡፡

የአዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ቦርድ ከቀረጻቸው የለውጥ ዕቅዶች መካከል የመጀመሪያ ምዕራፍ የሆነው የባንኩን ከፍተኛ አመራር ለውጥ ማካሄድን የሚመለከት ነው፡፡ ይህም የሚከናወነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በባንካችን ላይ በቅርቡ ባካሄደው ምርመራ ግኝት እና ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ነው፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በቀጣይ የሚያደርጉት ተጨማሪ ምርመራ እንደተጠበቀ ሆኖ በንብ እንተርናሽናል ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚነት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ገነነ ሩጋ ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል፡፡ በቀጣይም አዲሱ ቦርድ፣ የባንኩን አደረጃጀትና መዋቅር በማስተካከል ቀሪ የባንኩ ከፍተኛ ሥራ አመራር አባላትን ብቃትን መሠረት ባደረገ መስፈርት በመፈተሽ በአዲስ የመተካት ሥራ በማከናወን ባንኩን ወደ ነበረበት ከፍታ በአጭር ጊዜ የመመለስ ተግባሩን በተጠናከረ ሁኔታ ማካሄዱን ይቀጥላል፡፡

በሌላ በኩል ደንበኛ ተኮር የሆኑ አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶችን ማቅረብ ዋነኛ ተልዕኮው የሆነው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፤ የደንበኞችን ፍላጐት ማርካት ብሎም ተገቢውን አገልግሎት በሚፈለገው ጥራትና መጠን በማቅረብ አሁን ያጋጠመውን ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ በመቅረፍ ወደነበረበት ከፍታ ለመመለስ ቦርዱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ በመቀናጀት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል እንደሚሰራና ለመሳካቱም ቀን ከሌት እንደሚተጋ በዚሁ አጋጣሚ እያረጋገጠ ይህም እንደሚሳካ ሙሉ እምነት አለው፡፡

በመጨረሻም አዲሱ የንብ እንተርናሽናል ባንክ የዲሬክተሮች ቦርድ ባንኩ ካጋጠመው ችግር በአስቸኳይ እንዲላቀቅ የሚረዱ ተከታታይ የመፍትሔ እርምጃዎችን በመውሰድ የባንኩን ስምና ዝና ወደነበረበት ለመመለስ እንደሚተጋ በድጋሚ እያረጋገጠ፤ በዚህም ጉዞ የባንኩ ደንበኞች፣ ሠራተኞች፣ አስቀማጮች፣ ተበዳሪዎች፣ ባለአክሲዮኖች፣ ስመጥር ነጋዴዎች፣ የንግድ አጋሮቻችን፣ ሚዲያዎች እንዲሁም ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በሙሉ ከጎኑ እንደምትሰለፉ ያለውን ፅኑ ዕምነት እየገለፀ ለዚህም አስቀድሞ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡

 

የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ አ. ማ. የዳይሬክተሮች ቦርድ

የካቲት 7 ቀን 2ዐ16 ዓ. ም.

አዲስ አበባ

PDF File ለመመልከት ሊንኩን ይጫኑ => መግለጫ

NIB BANK

NIB BANK

Committed To Services Excellence

Share this post with

Recent Posts

News

ታታሪውን ባንካችን ወደ ደንበኞቹ ይበልጥ ለመቅረብ  “በአዲስ መንፈስ ለላቀ ከፍታ”

Read More

You May Also like

Reports

Jobs