Internet Banking
Internet Banking

አዲሷ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እመቤት መለሰ ዘለቀ(ዶ/ር) በይፋ ስራ ጀመሩ።

በቅርቡ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ሹመታቸው የፀደቀላቸው ዶክተር እመቤት ወደ ቢሯቸው ሲገቡ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። በአቀባበል ስነስርዓቱም የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ እና የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል።

 

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ”ወደ ንብ ባንክ የመጣሁት እናንተን በማገዝ ተቋሙን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ነው። ያለነው የተለየ መፍትሔ በሚሻ ጊዜ እንደመሆኑ የተለየ ርብርብና ቁርጠኝነት ያስፈልገናል” ብለዋል።

 

የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሺሰማ ሸዋነካ ለዋና ሥራ አስፈጻሚዋ የ”እንኳን ደህና መጡ” መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸውም ተመኝተዋል።

 

የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ባለአክሲዮኖች ታህሣሥ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደው 24ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ምርጫ የተመረጡት የቦርድ አባላት ባንኩን የማስተዳደር ተግባር ከጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ርክክብ በመፈጸም ወደስራ መግባታቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም፤ ቦርዱ ባንኩን ካጋጠሙት ተግዳሮቶች ለማውጣት በርካታ ሥራዎችን ለመስራት እንዲያስችለው ዕቅድ በመንደፍ ደረጃ በደረጃ ባንኩ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ስራዎችን አከናውኗል፡፡

 

ከእነዚህም መካከል የባንኩን ወቅታዊ ሁኔታ ለመረዳት እንዲያስችል በርካታ ውይይቶች ከባለድርሻ አካላት ጋር ያካሄደ ሲሆን፤ ከመድረኮቹም ጠቃሚ የሆኑ ግብዓቶች ተገኝተዋል፡፡ እንዲሁም የባንኩን የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገነነ ሩጋን ማሰናበቱ የሚታወስ ሲሆን፤ በጊዜያዊነት የባንኩን ስራ እንዲያስተባብሩ አቶ መልካሙ ሰለሞንን ተጠባባዊ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እንዲያገለግሉ አድርጓል፡፡

 

ከዚህም ጎን ለጎን ባንኩን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመራ ኃላፊ በማፈላለግ ላይ የነበረው ቦርዱ፤ ከቀረቡ ዕጩዎች መካከል እመቤት መለሰ ዘለቀ (ዶ/ር)ን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርጎ የመረጠ ሲሆን፤ ይኸው የዋና ሥራ አስፈጻሚ ሹመት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጸድቋል፡፡

 

እመቤት መለሰ ዘለቀ (ዶ/ር) ከ22 ዓመታት በላይ በባንኪንግ ኢንደስትሪ ውስጥ የሥራ ልምድ ያላቸው ሲሆን፤ እ.ኤ.አ. ከማርች 2022 ጀምሮ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስራቴጂ ፕላኒንግና ትራንስፎርሜሽን ምክትል ፕሬዚደንት ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

 

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአካውንቲንግ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአካውንቲንግና ፋይናንስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ እና ኤኮኖሚክስ ፋካልቲ ያገኙት እመቤት (ዶ/ር)፤ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን (ፒ.ኤች.ዲ.) በቢዝነስ ሊደርሺፕ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ስራ ትምህርት ቤት አግኝተዋል፡፡

 

በባንኪንግ ኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሙያ ሲሆኑ፤ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶችም ላይ አገልግለዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሪፎርም እና ትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት ቢሮን በምክትል ፕሬዚደንትነት (Vice President CBE Reform & Transformation Project Office)፣ ኮርፖሬት የሥራ ጥራት ማረጋገጥ (Vice President Corporate Quality Assurance)፣ የብድር ትንተና ምክትል ፕሬዚደንት (Vice President: Credit Appraisal)፤ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን ቀደም ብለውም በዛው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች በመምሪያ ኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

 

ዶ/ር እመቤት ታማኝ እና ታታሪ ባለሙያ መሆናቸውን በርካቶች ይመሰክሩላቸዋል፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቆይታቸው የነበራቸው አበርክቶ ቀላል የማይባል እንደነበረና ባንኩም ለደረሰበት ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው በኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉና የሚያውቋቸው ሲገልጹ ይደመጣል፡፡

 

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በቅርቡ ከሊኲዲቲ አስተዳደር (Liquidity Management) ጋር በተያያዘ ገጥሞት ከነበረው ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ በመውጣት ከጥሬ ገንዘብ ክፍያም ሆነ የRTGS ጋር በተያያዘ የነበሩት ችግሮች ሙሉ በሙሉ ከመቀረፋቸውም ባሻገር “በአዲስ መንፈስ ለላቀ ከፍታ!” በሚል መሪ ቃል እያካሄደ ባለው የማርኬቲንግ ንቅናቄ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበና ባንኩን ወደቀደመው ከፍታ ላይ ለመመለስ ብርቱ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡

 

ይህ በእንዲህ እዳለም የዶ/ር እመቤት በዋና ሥራ አስፈጻሚነት መሾም በተለይም አሁን በባንኩ እየታየ ያለውን ለውጥ፣ በደንበኞች፣ በሠራተኞችና በሌሎችም ባለድርሻ አካላት ዘንድ ያለውን መነቃቃት ቀጣይነት ከማረጋገጥና በአጠረ ጊዜ የባንኩን ስምና ዝና ወደነበረበት ከፍታ ከመመለስ ጋር ተያይዞ እየተሠራ ያለውን ሥራ የበለጠ እንደሚያጠናክረው ይታመናል፡፡

 

የንግድ እንቅስቃሴን በማሳለጥ ረገድ ለዓመታት የበኩሉን ድርሻ ሲወጣና የንግድ ማህረሰቡንም ሲያገለግል የቆየው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፤ ለ25 ዓመታት ያህል ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ያበረከተው አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

 

ጊዜያዊ ተግዳሮቶች አጋጥመውት የነበረ ቢሆንም፣ ባንኩ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ ለመሆኑ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ቀደም ሲል ጀምሮ በግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ ቋሚ ሀብት ማፍራቱ እንደአንድ ማሳያ ሊታይ የሚችል ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ወልቂጤ ከተማ የተገነባው ባለአምስት ወለል ህንጻ፣ ዱከም ከተማ የተገነባው ባለስድስት ወለል ህንጻ፣ ሆሳዕና ከተማ የሚገኘው ባለስድስት ወለል ህንጻ፣ አዲስ አበባ አራት ኪሎ የሚገኘው ባለስምንት ወለል ህንጻ፣ ባለ 14 ወለል የሐዋሳ ህንጻ፤ እንዲሁም አዲስ አበባ ሰንጋ ተራ አካባቢ ራስ አበበ አረጋይ ጎዳና የሚገኘውና በዲዛይኑም ሆነ በአሰራሩ ልዩ የሆነውና ባህላዊውን ምስለ-ንብ ቀፎ ባለ38 ወለል የዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ለተመልካች ልዩ መስህብ ከመሆኑም ባሻገር በአገርና በከተማ ደረጃ እንደ መለያ ምልክት ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

 

ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በነበሩ ውይይቶችም አዲሱ የባንኩ ቦርድ በተደጋጋሚ ባለፉት ጊዜያት ባጋጠመው ተግዳሮት ምክንያት እነዚህን ባለድርሻ አካላት ለደረሰባቸው መጉላላት ይቅርታ መጠየቁና፤ ባንኩን ከዚህ ችግር ለማላቀቅ አብረው በመስራት ድጋፋቸውን በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥሉ መጠየቁ ይታወሳል፡፡

 

በተጨማሪም፤ ባንኩን ለመረጃ ማዕከሉና ለሌሎች ሲስተሞቹ፤ ከዓለም አቀፍ የደህንነት ደረጃዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ፤ የኢንፎርሜሽን ደህንነት አስተዳደር የምስክር ወረቀት (የISO27001) ለማግኘት በንቃት በመሥራት ላይ ይገኛል። በአደጋ ግዜ ማገገምን እና የባንኩን ሥራዎች ቀጣይነት ለማረጋገጥ፣ ባንኩ ከአደጋ የማገገሚያ ማዕከሉን (Disaster Recovery Center) የማዘመን ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ይህም የባንኩን ያልተቋረጠ አገልግሎት በማቅረብ አቅም ከፍ አድርጎታል፡፡

 

በሌላ በኩል ባንኩ የደንበኞቹን ፍላጎት በተሻለ ደረጃ ለማሟላት የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያውን የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቶቹን ከፍ በሚያደርግ መልኩ አዘምኗል። በተጨማሪም፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና አገልግሎቶችን ከሞባይል ባንኪንግ ሲስተም ጋር ለማዋሃድ እንዲቻል ከተለያዩ ፊንቴክ ኩባንያዎች ጋር ትብብር ተመስርቷል።

 

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በሁሉም ቅርንጫፎቹ በተዘጋጁ ልዩ መስኮቶች እንዲሁም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብቻ በሚሰጡ የሃላል ቅርንጫፎቹ አማካኝነት የሸሪዓ ህግን መሰረት ያደረገ የተሟላ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት (የተለያዩ የተቀማጭና የኢንቨስትመንት አገልግሎቶችን) እየሰጠ ይገኛል፡፡

***

 

ይሠሯል ከልብ፣ እንደ ንብ!

 

NIB BANK

NIB BANK

Committed To Services Excellence

Share this post with

Recent Posts

News

ታታሪውን ባንካችን ወደ ደንበኞቹ ይበልጥ ለመቅረብ  “በአዲስ መንፈስ ለላቀ ከፍታ”

Read More

You May Also like

Reports

Jobs