በቅርቡ የተመረጡት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ሹመታቸው በብሔራዊ ባንክ ፀድቆ ባለፈው ሳምንት በይፋ ወደሥራ መግባታቸው ይታወሳል።
በቆይታቸው ከባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድና ማኔጅመንት አባላት እንዲሁም ከዲስትሪክት ሀላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል። በማስከተልም ከ2500 የአዲስ አበባ የባንኩ ቅርንጫፍ ሠራተኞች ጋር በአድዋ ሙዚየም የትውውቅ መርሐ-ግብር አካሂደዋል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር ”እኔ በዚህ ወቅት ወደ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ስመጣ እድለኝነት እየተሰማኝ ነው” ብለዋል። መላ ሠራተኛውም ”ባንኩ የኔ ነው። በስኬቱም ድርሻ አለኝ” ብሎ ሥራውን በአዲስ መንፈስ ሊያከናውን እንደሚገባ ተናግረዋል።
”ወደ ንብ ባንክ የመጣሁት ለለውጥ ነው” ያሉት ዶክተር እመቤት ባንኩ የሚያስፈልገውን ፈጣን ለውጥ ለማምጣት ሠራተኛው ትልቁ አጋዥ ሀይል ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በሠራተኛውም ሆነ በደንበኞቹ ተወዳጅ ባንክ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ባንኩ በአጭር ጊዜ ለውጥ እንዲያመጣ ተያይዞ መሥራት እንደሚገባ ገልፀዋል።
በመድረኩ አስተያየት የሰጡ ሠራተኞችም ባንኩ በጀመረው ለውጥ ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል። ባንኩ መውሰድ ስለሚጠበቅበት የማስተካከያ እርምጃዎች ዝርዝር አስተያየት የሰጡት ሠራተኞቹ ችግሮችን የሚያደምጥ አመራር ያስፈልገዋልም ብለዋል።
መድረኩን የመሩት የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሺሰማ ሸዋነካ እና ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ዶክተር እመቤት ከተሳታፊዎች ለተነሳው ጥያቄና አስተያየት ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተው መድረኩ ተጠናቋል።
***
ይሠሯል ከልብ፣ እንደ ንብ!