የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ 20ኛው መደበኛ የባለአክሲዮኖች ጉባኤ ኀዳር 27 ቀን 2012 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሄደ፡፡
የባንክ አገልግሎት አሰጣጡን ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሻሻልና ተደራሽነቱን በማስፋት የሚታወቀው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ለሃያ ዓመታት ደንበኞቹን በታታሪነት ሲያገለግል ቆይቷል፡፡
ባንኩ፣ የ3ኛው የአምስት ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅድና የአስር ዓመት ፍኖተ ካርታ አስጠንቶ ያዘጋጀ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ ሁለት ተጨማሪ የምክትል ፕሬዚደንት ቦታዎች፣ አዳዲስ መምሪያዎችና ሌሎች የሥራ መደቦችን የያዘ ድርጅታዊ መዋቅር ተግባራዊ አድርጓል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2018/19 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ባንኩ የሰጠው አጠቃላይ የብድር መጠን ብር 19.4 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ የተበዳሪዎች ቁጥርም ባለፈው በጀት ዓመት ከነበረው 11,626 ወደ 13,136 ከፍ ብሏል፡፡ የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ብር 27.7 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን አስቀማጭ ደንበኞች ቁጠርም ባለፈው ዓመት ከነበረው 679,178 በ196,239 በጨመር ወደ 875,417 ከፍ ብሏል፡፡ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የሠራተኞች ብዛት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 4,332 ወደ 4,972 ያደገ ሲሆን የቅርንጫፎች ቁጥርም 261 ደርሷል፡፡
የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ከአጠቃላይ የባንኩ ካፒታል ውስጥ 60 በመቶውን ድርሻ የያዘ ሲሆን መጠኑም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ27.6 በመቶ ጭማሪ በማሳየት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ብር 2.65 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ ባንካችን በበጀት ዓመቱም ከፍተኛ ትርፍ አስመዝግቧል፡፡
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ከባንክ አገልግሎቱ በተጨማሪ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ለዋና መ/ቤት፣ ለቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችና ለሌሎች ዓላማዎች የሚያገለግሉ ግንባታዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት በሰንጋ ተራ የሚገነባውና ለከተማው ከፍተኛ ውበት እየሰጠ የሚገኘው ባለ 4B+G+32 ወለል የዋና መ/ቤት ሕንጻ ግንባታ በጥሩ አፈጻጸም አረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ይጠናቀቃል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ በሆሳዕና ከተማ የሚገኘው ባለ 4 ፎቅ ሕንጻ ግንባታ ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በጨረታ የተገዛው የአራት ኪሎው ሕንጻ ደግሞ ሙሉ በሙሉ በቅርቡ ይጠናቀቃል፡፡ በሐዋሳ እየተገነባ ያለው መንትያ ሁለገብ ሕንጻ በከተማው ውስጥ የባንኩን ገጽታ ከፍ አድርጎ እያሳየ ያለ ፕሮጀክት ነው፡፡
ባንኩ በሚቀርቡለት የድጋፍ ጥሪዎች መሠረትና በራስ ተነሳሽነት የተለያዩ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡ በዚህ መሠረት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ብቻ የተለያዩ አገራዊ ተልእኮዎችና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የማኀበረሰብ ክፍሎች ብር 16.7 ሚሊዮን ድጋፍ አድርጓል፡፡
ባንኩ በቀጣይም ዘላቂ ትርፋማ ዕድገት ማስመዝገብ፣ የላቀ የደንበኞች አገልሎት ማስፈን፣ በተነሳሽነትና በባለቤትነት መንፈስ የሚሠራ የሰው ኃይል መፍጠር እና ጠንካራ የገቨርናንስና ስጋት መከላከል ባህል መገንባት የሚሉትን ተፈጻሚ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ከበንኩ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡
በሂደት ላይ የሚገኙትን የሕንጻ ግንባታዎችም በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቁ ለማድረግ ያላሰለሰ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና የባንኩ መልካም ሥምና ተቀባይነት የማሳደግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በ2019/20
2
በጀት ዓመት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የኮር ባንኪንግ ሲስተምን የማሻሻል ሥራና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ቅርንጫፍ የማስፋፋት ሥራ ይገኙበታል፡፡
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ የተሻሻሉ የቁጠባ አይነቶችን በማስተዋዋቅ በርካታ ደንበኞችን አፍርቷል፡፡ ከውጭ አገር ከዘመድ ወዳጅ ገንዘብ ለሚላክላቸው ወይም ለሚቀበሉ ከዘመናዊ የቤት አውቶሞቢል ጀምሮ ባለ ዕድል የሚያደርጉ ከ100 በላይ የሎተሪ ዕጣዎችን ለሁለተኛ ጊዜ አዘጋጅቶ አሸናፊዎችን ሸልሟል፡፡
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተደራሽነቱን በማስፋትና የቅርንጫፎቹን ቁጥር በማሳደግ መሪና የሁሉም ኢትዮጵያውያን ባንክ የመሆን ጥረቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ለበርካታ ደንበኞችም የፋይናንስ ፍላጎታቸውን በቅርብ ተገኝቶ በመቅረፍ በአገሪቱ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ላይ አዎንታዊ ሚናውን በመጫወት ለዕድገት ጉልህ ድርሻ በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡
በመጨረሻም አሁን በመምራት ላይ ያለው ቦርድ የሥራ ጊዜ በሚቀጥለው ዓመት ስለሚያበቃ ባንኩን ሊመሩ የሚችሉ የቦርድ አባላት አስመራጭ ኮሚቴ ተመርጦ ጉባኤው ተጠናቋል፡፡