ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በአገራችንና በዓለም አቀፍ ደረጃ በመስፋፋት ላይ የሚገኘው የኮረና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝ በዜጎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ በመመልከት   የወለድ ምጣኔ ቅናሽ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

በቫይረሱ ተጽዕኖ በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂ በሆኑ የኢኮኖሚ  ዘርፎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የባንኩ ተበዳሪዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት የባንኩ ቦርድና ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚ ባደረገው ስብሰባ፦ ለሆቴልና ቱሪዝም፣ ለአስጎብኚ ድርጅቶች፣ ለአበባ አትክልትና ፍራፍሬ እርሻ ተበዳሪዎች ከግንቦት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ወራት የሚቆይ የወለድ ምጣኔ ቅናሽ እንዲደረግ ወስኗል፡፡

በዚህም መሠረት የኮረና ቫይረስ ከመከሰቱ በፊት ካደረገው እስከ 4.5 በመቶ ከሚሆን የወለድ ቅናሽ በተጨማሪ ለሆቴልና ቱሪዝም ሶስት በመቶ ቅናሽ አድርጓል፡፡ የአትክልት የአበባና ፍራፍሬ እርሻ ኢንቨስትመንቶችን በተመለከተም ባንኩ ከእነዚህ ዘርፎች ሊያገኝ የሚገባውን የትርፍ ህዳግ በመተው የወለድ ተመኑ ላይ ቅናሽ በማድረግ በመደበኛ የተቀማጭ ገንዘብ ላይ በሚታሰብ የሰባት በመቶ ወለድ እንዲሆን ወስኗል፡፡  

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ የተበዳሪዎች ጥያቄን መሠረት በማድረግ የብድር መክፈያ ጊዜን አራዝሟል፡፡ ባንኩ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንጻርም ወረርሽኙን በአገር አቀፍ ደረጃ ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ብር 5,000,000.00 (አምስት ሚሊዮን ብር) ለብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ድጋፍ ማድረጉ ይታወቃል፡፡

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ኮረና ቫይረስን በአግባቡ ለመከላከል እንዲቻል ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በባንኩ የበላይ አመራር የሚመራ አስተባባሪ ኮሚቴ ያቋቋመ ሲሆን፤ ከሠራቸው ሥራዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

 • በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤትና በሁሉም ቅርንጫፎች ቫይረሱን የሚመለከቱ የጽሑፍ ማሳሰቢያዎችና ማስጠንቀቂያዎች ተለጥፈዋል፡፡
 • ለሁሉም ሠራተኞች ሳሙና፣ አልኮል፣ ሳኒታይዘር፣ ጓንት፣ ፎጣና ማስክ….. ታድሏል፡፡
 • ለደንበኞችና ለሠራተኞች በቅርንጫፎች፣ በዋናው መሥሪያ ቤትና የባንኩ ሕንጻዎች ባሉበት ሁሉ የተሟሉ የእጅ መታጠቢያዎች ተዘጋጅተዋል፡፡
 • በቅርንጫፎች ሁሉ በአንድ መስኮት አንድ ሰው ብቻ ሆኖ አስተናጋጅና ተስተናጋጅ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲገለገሉ ተመቻችቷል፡፡
 • አካላዊ መቀራረብ እንዳይኖር ደንበኞች በባንኩ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች በኤቲኤም፣ ፖስ፣ ሞባይልና ኢንተርኔት ባንኪንግ እንዲጠቀሙ ተደርጓል፡፡ ይህንንም ለማበረታታት የኤቲኤም የአገልግሎት ክፍያ ነጻ እንዲሆን ከመደረጉም ባሻገር በዚሁ ቴክኖሎጂ በመጠቀም እስከ ብር 10,000.00 ማውጣት እንዲሁም በሞባይል እስከ 30,000.00 በኢንተርኔት ለመደበኛ ደንበኞች 100,000.00 ለኮርፖሬት ደንበኞች 500,000.00 ማስተላለፍ እንዲችሉ ተደርጓል፡፡
 • ባንካችን ለባንክ መተማመኛ ሰነድ (L/C) ማራዘሚያ የሚያስከፍለውን ኮሚሽን አስቀርቷል፡፡ እንዲሁም በቀጥታ ገንዘብ ክፍያ አማካኝነት ዕቃ ለሚያስገቡ (CAD) ደንበኞች ይከፈል የነበረውን የአገልግሎት ክፍያ ማራዘሚያ በ50 በመቶ ቀንሷል፡፡
 • በባንኩ ለሚሠሩ ሕመም ያለባቸው፣ የሚሠሩበት ክፍል መጨናነቅ ያለበትና በዕድሜ የገፉ ሠራተኞች በቅድሚያ ፈቃድ እንዲወጡና ሌሎች ሠራተኞችም በፈረቃ እንዲሠሩ ተደርጓል፡፡
 • የባንኩ ሠራተኞች በዚህ ቫይረስ ምክንያት ሊከሰትባቸው የሚችለው የኢኮኖሚ ተጽዕኖ ለመከላከል የሁለት ወር የብድር ክፍያቸው እንዲራዘም ተደርጓል፡፡
 • በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት የተፈጠረውን መዘናጋት ለማስወገድ ሠራተኞች ከጤና ተቋማት የሚሰጡ መመሪያዎች በአግባቡ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥብቅ ትእዛዝ የተላለፈ ሲሆን በቅርንጫፎችና በኤቲኤም ማሽኖች ዙሪያም የንጽህና ሥራ እንዲሠራ ተደርጓል፡፡
 • የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማዳበር የተለያዩ ማስታወቂያዎች ተሠርተው በሚዲያ ተሰራጭተዋል፡፡
 • የኮረና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ከአንድ ለትርፍ ካልተቋቋመ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመሆን በአዲስ አበባ በአስሩም ክፍለ ከተሞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡  
 • መንግሥት ባቀረበው ጥሪ መሠረት የቫይረሱ ወረርሽኝን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ለሚፈልጉ በባንኩ የሂሣብ ቁጥር 7000016792239 ተከፍቷል፡፡