በኢትዮጵያ የግል ባንኮች ታሪክ ቀደምት አሻራቸውን ካሳረፉት መካከል አንዱ የሆነው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ከምስረታው ጀምሮ ለተከታታይ ሃያ ዓመታት የትርፍ መጠኑን እያሳደገ መጥቶ  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት (እ.አ.አ 2019/20) ከታክስና ከተለያዩ ቅንስናሾች በፊት ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ በማትረፍ በሀገሪቱ በትርፍ ቀዳሚ ከሚባሉ ባንኮች አንዱ መሆኑን በድጋሚ አረጋግጧል፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ላይ ያሳደረውን ተግዳሮት ተቋቁሞ ይህንን ትልቅ ትርፍ ለማስመዝገብ ችሏል፡፡ የተመዘገበው የትርፍ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በብር 378.3 ሚሊዮን ወይም 36.9 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በቀጣይም ከዚህ የተሻለ አመርቂ ትርፍ ለማስመዝገብ ተግቶ እንደሚሠራ ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከባንኩ በተገኘው ግርድፍ የሂሣብ መረጃ መሠረት የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ 33.2 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ከአምናው 27.6 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር የ21.5 በመቶ ዕድገት ለማሳካት ተችሏል፡፡ የባንኩ አጠቃላይ ሐብት 42 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ከአምናው 33.5 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር የ25.1 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ የተከፈለ ካፒታል ከብር 2.6 ቢሊዮን ወደ ብር 3.4 ቢሊዮን ያደገ ሲሆን አጠቃላይ ካፒታልና መጠባበቂያም ከብር 4.4 ቢሊዮን ወደ ብር 5.8 ቢሊዮን በማሳደግ መሪ ከሆኑት የግል ባንኮች መካከል አንዱ የመሆን ዕቅዱን ለማሳካት ጥረቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡        

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተደራሽነቱን በማስፋትና የቅርንጫፎቹን ቁጥር ከሶስት መቶ በላይ እንዲሁም የደንበኞቹን ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ በላይ አድርሷል፡፡ ለበርካታ ደንበኞችም የፋይናንስ ችግራቸውን በመቅረፍ በአገሪቱ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ላይ አዎንታዊ ሚናውን በመጫወት ለዕድገት ጉልህ ድርሻ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ ባንኩ፣ በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ የተለያዩ የቁጠባ አይነቶችን በማስተዋዋቅ በርካታ ደንበኞችን አፍርቷል፡፡    

ባንካችን፣ የኮረና ቫይረስን ለመከላከል በሀገር ደረጃ እና በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በኩል ለሚደረገው ጥረት እንዲያግዝ ከብር 5.1 ሚሊዮን በላይ የለገሰ ሲሆን ለባንኩ ተበዳሪዎችና ሌሎች ደንበኞች የወለድ ምጣኔን፣ እንዲሁም የተለያዩ ክፍያዎችን በመቀነስና አንዳንዶቹንም በመሰረዝ ከእነዚህ በአጠቃላይ ሊያገኝ ይችል የነበረውን ከብር 113 ሚሊዮን በላይ ገቢ በመተው ሀገራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድ በታላቅ ደረጃ አጋርነቱን አሳይቷል፡፡

አካላዊ መቀራረብ እንዳይኖር ደንበኞች በባንኩ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች በኤቲኤም፣ ፖስ፣ ሞባይልና ኢንተርኔት ባንኪንግ እንዲጠቀሙ የተመቻቸ ሲሆን ይህንንም ለማበረታታት የኤቲኤም የአገልግሎት ክፍያ ነጻ እንዲሆን ከማድረጉም ባሻገር በዚሁ ቴክኖሎጂ በመጠቀም እስከ ብር 10,000.00 ማውጣት እንዲሁም በሞባይል እስከ ብር 30,000.00፣ በኢንተርኔት ለመደበኛ ደንበኞች ብር 100,000.00 እና ለኮርፖሬት ደንበኞች ብር 500,000.00 ማስተላለፍ እንዲችሉ ተደርጓል፡፡  

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንጻር ለሸገር ማስዋቢያ ፕሮጀክት ብር 10 ሚሊዮን፣ ለአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የትምህርት መሣሪያ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ  ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ባንኩ “ይሠሯል ከልብ፣ እንደ ንብ!” የሚለውን መሪ ቃል ያነገበ የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን አዘጋጅቶ በትግበራ ላይ የሚገኝ ሲሆን በዚህም የኮር ባንኪንግ ስርአቱን እጅግ ዘመናዊ በሆነው የT24 Version 2020 ቴክኖሎጂ፣ Tier 3 data center እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችንም በመጠቀም ለደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ይገኛል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ለመዲናችን አዲስ አበባ ብሎም ለሀገራችን የገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችለውን ከፍታው ባለ 4B+G+M+32 የሆነው የዋናው መሥሪያ ቤት ሕንጻ በቅርቡ ለመጨረስ እየተዘጋጀ ሲሆን፤ ለአራት ኪሎ አካባቢ ውበት ያጎናጸፈው ባለ 2B+G+7 የሆነው የአራት ኪሎ ሕንጻውን በማጠናቀቅና በዚሁ ሕንጻ ላይ የፕሪሚየም ቅርንጫፉን በመክፈት ደንበኞቹን በላቀ ደረጃና ክብር ለማገልገል  ተግቶ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

ባንኩ የዕድገት ጉዞውን በፈጣን ሁኔታ እያከናወነ ሲሆን ለዚህ ውጤት እንዲበቃ ላደረጉት ለባንኩ የቦርድ አመራሮች፣ ማኔጅመንትና መላው ሠራተኞች እንዲሁም ለውድ ደንበኞቹ ከፍተኛ ምስጋና እያቀረበ፤ ወደፊትም ከዚህ በበለጠ በመሥራት ለሀገርና ለወገን አኩሪ ተግባር ለመፈጸም እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጿል፡፡    

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ

ይሠሯል ከልብ እንደ ንብ!