ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝ በኢኮኖሚው ዘርፍ ላይ ያደረሰውን ጉዳት በመመልከት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩ የባንኩ ደንበኞችን ለመደገፍ በድጋሚ የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሽ አደረገ፡፡

በአገር ውስጥ ንግድ፣ በሕንጻና ኮንስትራክሽን፣ በአምራችነት፣ በአስመጪነት፣ በፕሮጀክት ደረጃ ላሉ ሆቴሎች፣ በትራንስፖርት፣ በማዕድን ኢነርጂና ውኃ፣ በግብርናና በግል ዘርፍ ለተሰማሩ የባንኩ ተበዳሪዎች እስከ ሶስት ወራት የሚቆይ የ0.5 በመቶ የወለድ ምጣኔ ቅናሽ እንዲደረግ የባንኩ ቦርድና ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚ ወስኗል፡፡ ባንኩ እስካሁን ያደረገው የወለድ ቅናሽ ከ113 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚያሳጣው አስታውቋል፡፡

ቀደም ሲልም ለባንክ መተማመኛ ሰነድ (L/C) ማራዘሚያ የሚያስከፍለውን ኮሚሽን ሙሉ በሙሉ ነጻ ያደረገ ሲሆን በቀጥታ ገንዘብ ክፍያ አማካኝነት ዕቃ ለሚያስገቡ (CAD) ደንበኞች ይከፈል የነበረውን የአገልግሎት ክፍያ ማራዘሚያም በ50 በመቶ ቀንሷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባንኩ ለደንበኞቹ ያስከፍል የነበረውን የኤቲኤም አገልግሎት ክፍያ ነጻ አድርጓል፡፡

የኮረና ቫይረስ ከመከሰቱ በፊት ካደረገው እስከ 4.5 በመቶ ከሚሆን የወለድ ቅናሽ በተጨማሪ ከግንቦት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ወራት የሚቆይ፦ ለሆቴልና ቱሪዝም ሶስት በመቶ፣ የአትክልት የአበባና ፍራፍሬ እርሻ ኢንቨስትመንቶችን በተመለከተም ባንኩ ከእነዚህ ዘርፎች ሊያገኝ የሚገባውን የትርፍ ህዳግ በመተው የወለድ ተመኑ ላይ ቅናሽ በማድረግ በመደበኛ የተቀማጭ ገንዘብ ላይ በሚታሰብ የሰባት በመቶ ወለድ እንዲሆን ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንጻርም ወረርሽኙን በአገር አቀፍ ደረጃ ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ብር 5,000,000.00 (አምስት ሚሊዮን ብር) ለብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ መለገሱንና ቫይረሱን በሚገባ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለመጨመር በአዲስ አበባ በአስሩም ክፍለ ከተሞች የጥንቃቄ መልዕክቶች እንዲተላለፍ አድርጓል፡፡

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ኮረና ቫይረስን በአግባቡ ለመከላከል እንዲቻል ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በባንኩ የበላይ አመራር የሚመራ አስተባባሪ ኮሚቴ ያቋቋመ ሲሆን፤ ከሠራቸው ሥራዎች መካከል  ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

  • በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤትና በሁሉም ቅርንጫፎች ቫይረሱን የሚመለከቱ የጽሑፍ ማሳሰቢያዎችና ማስጠንቀቂያዎች ተለጥፈዋል፡፡
  • ለሁሉም ሠራተኞች ሳሙና፣ አልኮል፣ ሳኒታይዘር፣ ጓንት፣ ፎጣና ማስክ ታድሏል፡፡
  • ለደንበኞችና ለሠራተኞች በቅርንጫፎች፣ በዋናው መሥሪያ ቤትና የባንኩ ሕንጻዎች ባሉበት ሁሉ የተሟሉ የእጅ መታጠቢያዎች ተዘጋጅተዋል፡፡
  • በቅርንጫፎች ሁሉ በአንድ መስኮት አንድ ሰው ብቻ ሆኖ አስተናጋጅና ተስተናጋጅ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲገለገሉ ተመቻችቷል፡፡
  • አካላዊ መቀራረብ እንዳይኖር ደንበኞች በባንኩ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች በኤቲኤም፣ ፖስ፣ ሞባይልና ኢንተርኔት ባንኪንግ እንዲጠቀሙ ተደርጓል፡፡ ይህንንም ለማበረታታት የኤቲኤም የአገልግሎት ክፍያ ነጻ እንዲሆን ከመደረጉም ባሻገር በዚሁ ቴክኖሎጂ በመጠቀም እስከ ብር 10,000.00 ማውጣት እንዲሁም በሞባይል እስከ 30,000.00 በኢንተርኔት ለመደበኛ ደንበኞች 100,000.00 ለኮርፖሬት ደንበኞች 500,000.00 ማስተላለፍ እንዲችሉ ተደርጓል፡፡
  • የባንካችን ሠራተኞችም ሆኑ ደንበኞች የአፍ መሸፈኛ ጭንብል አድርገውና እጃቸውን በአግባቡ አጽድተው ቢሮ እንዲገቡ ከፍተኛ ቁጥጥር እያደረገ ይገኛል፡፡