ፕሬስ ሪሊዝ፣

ታህሳስ 5 ቀን 2014 ዓ.ም

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ብር 1.68 ቢሊዮን ትርፍ አስመዘገበ

  • የካፒታል መጠኑንም ወደ 10 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ተወሰነ
  • የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻ ውበትና ዘመናዊነት ተወደሰ

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ባሳለፍነው የበጀት ዓመት ከገቢ ግብርና ለብድር ከሚያዝ መጠባበቂያ በፊት ብር 1.68 ቢሊዮን በማስመዝገብ በአገሪቱ በውጤታማነት ከሚታወቁት አንጋፋ የግል ባንኮች አንዱ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የባንኩ የባለአክስዮኖች 22ኛው መደበኛና 18ኛው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ፣ ማክሰኞ ታህሳስ 5 ቀን 2014 ዓ.ም ከጧቱ 2፡30 ሰዓት ጀምሮ ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው ኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል በተካሄደበት ወቅት ነበር፡፡

ጉባዔው፣ እስከ ኅዳር 30 ቀን 2014 ዓ.ም የተካሄዱ አዳዲስ የአክስዮን ግዢና ዝውውሮችን በመቀበል፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና የውጭ ኦዲተሮች  የ2020/21 በጀት ዓመት ሪፖርት ሰምቶና ተወያይቶ አጽድቋል፡፡ በተጨማሪም የቦርድ አባላት ዓመታዊ የሥራ ዋጋና ወርሃዊ አበል የተወሰነ ሲሆን፤ በዲሬክተሮች ቦርድ በቀረበው የዘመኑ የተጣራ ትርፍ አደላደልና አከፋፈል የውሣኔ ሃሳብ እንዲሁም በውጭ ኦዲተሮች ሹመት ላይ ተወያይቶ በማጽደቅ ክፍያቸውንም ወስኗል፡፡

በዚህ የስብሰባ ወቅት በአስቸኳይ ጉባዔ መርሃ ግብሩ መሠረት የባንኩን የካፒታል መጠን ከ5 ቢሊዮን ወደ 10 ቢሊዮን ለማሳደግ ውሳኔ ላይ ተደርሷል፤ በዚህም ባንኩ በካፒታል ረገድ ቀዳሚ ከሚባሉ ባንኮች ተርታ መሰለፉን ተገልጿል፡፡ 

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ አ.ማ ግንቦት 19 ቀን 1991 ዓ.ም በ717 ባለ አክስዮኖች፣ በ27.6 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ተመስርቶ፣ በሃያ ሰባት ሠራተኞች በሾላ ቅርንጫፍ የዛሬ 22 ዓመት ጥቅምት 18 ቀን 1992 ዓ.ም በይፋ ሥራ የጀመረ መሆኑ ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ እ.ኤ.አ በጁን 30 ቀን 2021 በተጠናቀቀው በጀት የተከፈለ ካፒታሉን ወደ ብር 4.3 ቢሊየን፣ የተቀማጭ ገንዘቡን ወደ ብር 43.2 ቢሊየን፣  የብድር መጠኑን ብር 34.5 ቢሊየን  እንዲሁም የትርፍ መጠኑን ከገቢ ግብርና ለብድር ከሚያዝ መጠባበቂያ በፊት ብር 1.68 ቢሊዮን አድርሷል፡፡ ባንኩ ከ7,380 በላይ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን የቅርንጫፍ አድማሱንም በማስፋት ከ380 በላይ ቅርንጫፎችን በመክፈት ለውድ ደንበኞቹ ብቁ በሆኑ ሰራተኞች አማካኝነት ዘመኑ ያፈራዉን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተቀላጠፈ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ግንባር ቀደም ባንክ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በምስለ ንብ ቀፎ ዲዛይን ያስገነባው ባለ 37 ወለል ሰማይ ጠቀስ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻ በርዝመቱም ሆነ በዘመናዊነቱ ብሎም በውበቱ እጅግ ድንቅ የሆነ የገጽታ ግንባታ ለከተማችንና ለአገራችን የሚሰጥ ከመሆኑ ባሻገር በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሚያዚያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ሥራ በማስጀመር ለአገልግሎት ማብቃቱም በስብሰባው ወቅት ተገልጿል፡፡

ባንኩ ለመዲናችን እንዲሁም ለአገራችን የገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሕንጻ ከመገንባቱ በተጨማሪ በቴክኖሎጂም ረገድ የቅርብ ጊዜ ስሪት የሆነው የT24 ኮር ባንኪንግ ሲስተም በመዘርጋት ለደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

በዚህም አጋጣሚ ባንኩ እየተጠቀመበት ያለው የቴክኖሎጂ ሥርአት ወደ ዘመናዊ ስሪት በሚቀይርበት ወቅት በደንበኞች በኩል ለተፈጠረው መጉላላት ከፍተኛ ይቅርታ የተጠየቀ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ችግሩ ተስተካክሎ ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ

ይሠሯል ከልብ፣ እንደ ንብ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *