የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ 21ኛው መደበኛ የባለአክስዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ታህሳስ 15 ቀን 2013 ዓ.ም በኢንተርኮንትኔንታል አዲስ ሆቴል አዳራሽ በተካሄደበት ወቅት፤ ባንኩ በስትራቴጂክ ፕላኑ በአምስተኛው ዓመት ይደርስበታል ተብሎ የታቀደውን የትርፋማነት መስፈርት በ2 ዓመት ጊዜ ውስጥ በማሳካት 1.3 ቢሊዮን ብር አትርፎ በኢንዱስትሪው ውስጥ ካሉ ቀዳሚ ከሚባሉ የግል ባንኮች አንዱ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

የአገልግሎት አሰጣጡን ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሻሻልና ተደራሽነቱን በማስፋት የሚታወቀው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ለሃያ አንድ ዓመታት ደንበኞቹን ይሠሯል ከልብ፣ እንደ ንብ! በሚለው መሪ ቃል በታታሪነት የሚያገለግል መሆኑ ተገልጿል፡፡

ባንኩ፣  በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የሠራተኞች ብዛት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው   4,972 ወደ 5,934 ያደገ ሲሆን የቅርንጫፎች ቁጥርም ከ300 በላይ ሆኗል፡፡ እ.ኤ.አ በ2019/20 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ባንኩ የሰጠው አጠቃላይ የብድር መጠን ብር 25.8 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ የተበዳሪዎች ቁጥርም ባለፈው በጀት ዓመት ከነበረው 13,136 ወደ 15,541 ከፍ ብሏል፡፡ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ የተሰጠው የብድር ክምችት ከአጠቃላይ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ጋር ሲነጻጸር 77 በመቶ የደረሰ ሲሆን ባለፈው በጀት ዓመት ከነበረው 70 በመቶ አኳያ የ7 በመቶ መሻሻል አሳይቷል፡፡ የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ብር 33.7 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን የአስቀማጭ ደንበኞች ቁጥርም ባለፈው ዓመት ከነበረው 875,338 በ332,657 በመጨመር ወደ 1,207,995 ከፍ ብሏል፡፡

የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ከአጠቃላይ የባንኩ ካፒታል ውስጥ 59.4 በመቶውን ድርሻ የያዘ ሲሆን መጠኑም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ29.7 በመቶ ጭማሪ በማሳየት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ብር 3.44 ቢሊዮን ደርሷል፡፡

የባንኩ የዘመኑ ትርፍ ከገቢ ግብርና ለብድር ከሚያዝ መጠባበቂያ በፊት ብር 1.31 ቢሊዮን ሲሆን ይህም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ተመዝግቦ ከነበረው 928.4 ሚሊዮን ጋር ሲነጻጸር የብር 381.2 ሚሊዮን ወይም 41.1 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ የትርፍ ዕድገቱም በባንኩ ስትራቴጂክ ፕላን ላይ ከተቀመጠው የ40 በመቶ ዕድገት በላይ በመሆኑ የባንኩ ውጤታማነት አመርቂ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ባንኩ በዚህ ዓመት ያስመዘገበው አጠቃላይ ገቢ ብር 4.55 ቢሊዮን ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የብር 1.2 ቢሊዮን ወይም የ36.2 በመቶ የገቢ ዕድገት ያስመዘገበ በመሆኑ በበጀት ዓመቱ ላቅ ያለ ትርፍ ካስመዘገቡ ግንባር ቀደም ባንኮች አንዱ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ከባንክ አገልግሎት በተጨማሪ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ለዋና መ/ቤት፣ ለቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችና ለሌሎች ዓላማዎች የሚያገለግሉ የሕንጻ ግንባታዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት በሰንጋ ተራ የሚገነባውና ለከተማው ከፍተኛ ውበት እየሰጠ የሚገኘው ባለ 4B+G+32 ወለል የዋና መ/ቤት ሕንጻ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን፤ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሥራ ይጀምራል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ የወልቂጤ፣ የዱከም፣ የሆሳዕናና የአራት ኪሎ ሕንጻዎች ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን በሐዋሳ እየተገነባ ያለው መንትያ ሁለገብ ሕንጻ የግንባታ ሥራው በመፋጠን ላይ ይገኛል፡፡

ባንኩ በሚቀርቡለት የድጋፍ ጥሪዎች መሠረትና በራስ ተነሳሽነት የተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ሕዝባዊ ተቋማትን በመደገፍ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡ በዚህ መሠረት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ብቻ ለገበታ ለሸገር፣ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢኮኖሚና በኅብረተሰቡ ላይ ያስከተለውን ከፍተኛ ተጽዕኖ ለመቋቋም በአገር ደረጃ ለተደረገው ጥሪ ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በድምሩ ብር 21.9 ሚሊዮን ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፤ ለባንኩ ደንበኞች የብድር ወለድና የሌሎች አገልግሎቶች ክፍያዎች ስረዛና ቅናሽ በማድረግ ለአገርና ለንግዱ ማኅበረሰብ አጋርነቱን አሳይቷል፡፡ የኮረና ቫይረስን ምክንያት በማድረግ ለባንኩ ተበዳሪዎችና ሌሎች ደንበኞች የወለድ ምጣኔን፣ እንዲሁም የተለያዩ የአገልግሎት ክፍያዎችን በመቀነስና አንዳንዶቹንም በመሰረዝ ከእነዚህ በአጠቃላይ ሊያገኝ ይችል የነበረውን ከብር 113 ሚሊዮን በላይ ገቢ በመተው አገራዊ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡፡

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ የተሻሻሉ የቁጠባ አይነቶችን በማስተዋወቅ በርካታ ደንበኞችን አፍርቷል፡፡ ከውጭ አገር ከዘመድ ወዳጅ ገንዘብ ለሚላክላቸው ወይም ለሚቀበሉ ከዘመናዊ የቤት አውቶሞቢል ጀምሮ ባለዕድል የሚያደርጉ ከ100 በላይ የሎተሪ ዕጣዎችን አዘጋጅቶ ለአሸናፊዎች ለሶስተኛ ጊዜ የሸለመ ሲሆን፤ በቅርቡም “እንሸላለም” በሚል መርሃ ግብር በባንኩ ቅርንጫፎች ለሚቆጥቡ ደንበኞች አንድ አይሱዙ የጭነት መኪና፣  ባጃጆች፣ የውኃ ፓምፖችና ስማርት የሞባይል ቀፎዎች ለመሸለም ተዘጋጅቷል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ በምትታወቅበት ሉሲ በሚል ስያሜ ለሴቶች የቁጠባ ሂሣብ በማዘጋጀት የመጀመሪያ የግል ባንክ ሲሆን፤ በዚህም የሴቶችን ተሳትፎ ለማበረታታት እጅግ አጓጊ የሆኑ ሽልማቶች የያዘ መርሃ ግብር አዘጋጅቷል፡፡

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ለደንበኞች የሚሰጠውን አገልግሎትና ተደራሽነቱን ለማስፋት የቅርንጫፎቹን ቁጥር በማሳደግ መሪና የሁሉም ኢትዮጵያውያን ባንክ የመሆን ጥረቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ለበርካታ ደንበኞችም የፋይናንስ ፍላጎታቸውን በቅርብ ተገኝቶ በመቅረፍ በአገሪቱ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ላይ አዎንታዊ ሚናውን በመጫወት ለዕድገት ጉልህ ድርሻ በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

በመጨረሻም ባንኩን በመምራት ላይ የነበረው የዲሬክተሮች ቦርድ የሥራ ጊዜው ስለተጠናቀቀ በሚቀጥለው ጊዜ ባንኩን ሊመሩ የሚችሉ የቦርድ አባላት ተመርጠው ጉባዔው ተጠናቋል፡፡

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ለንግድ እጅግ በጣም ቅርብ በሆኑ የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልጽግና ለማሳካት በሚጥሩ 717 ባለአክስዮኖች ተቋቁሞ፣ በ27.6 ሚሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል፣ በ27 ሠራተኞች ጥቅምት 18 ቀን 1992 ዓ.ም ሥራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ይጠቀምበት ከነበረው የንብ ምልክትና ሥም ጋር በተያያዘ አንዳንድ ሰዎች ከቀድሞው ገዢ ፓርቲ ጋር ያያይዙት እንደነበረ፣ ነገር ግን ባንኩ እጅግ ታታሪ በሆኑ ሥራ ወዳድ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ያልወገነና በፓርቲ ባለቤትነት ያልተያዘ ትኩረቱም በባንክ አገልግሎት ላይ አድርጎ የሚንቀሳቀስና በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ላይ የማይደራደር የግል የፋይናንስ ተቋም እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ

ይሠሯል ከልብ፣ እንደ ንብ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *