Internet Banking
Internet Banking

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ተከታታይነት ያለው ስኬት ማስመዝገቡን አጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ

ፕሬስ ሪሊዝ

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በርካታ በአለም አቀፍ ደረጃና በአገር ውስጥ የተከሰቱ የኢኮኖሚና ንግድ እንቅስቃሴ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ያልተቋረጠና ተከታታይነት ያለው ውጤታማነቱን በተጠናቀቀው 2021/22 የበጀት ዓመትም አጠናክሮ ማስቀጠሉን ተገለፀ፡፡

በዚህም መሰረት ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በበጀት ዓመቱ ከግብር በፊት ብር 1.76 ቢሊዮን ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን ከቀደመው ተመሳሳይ የበጀት ዓመት ወቅት ጋር ሲነፃፃር የ139.3 ሚሊዮን ጭማሪ ማሳየቱ ተጠቁሟል፡፡

የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የብር 6.22 ቢሊዮን ወይም የ 14.3 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ብር 49.76 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ የብድር ክምችት በተመሳሳይ መልኩ አምና ከነበረው በብር 5.2 ቢሊዮን ወይም የ15.2 በመቶ በማደግ ብር 39.4 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ሃብት አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው በብር 7.3 ቢሊዮን ወይም 13.45 በመቶ በመጨመር በሰኔ 3ዐ ቀን 2ዐ22 ብር 61.49 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ በሌላ በኩል የባንኩ የተከፈለ ካፒታል በበጀት ዓመቱ የ13.24 በመቶ ጭማሪ በማስመዝገብ ብር 4.82 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ጠቅላላ ካፒታልና መጠባበቂያ ሂሣብ መጠን ደግሞ ብር 8.1 ቢሊዮን ደርሷል፡፡

ባንኩ በበጀት ዓመቱ ካስመዘገበው ከላይ ከተገለፁት አበረታች የፋይናንስ እንቅስቃሴና ውጤት ባሻገር ሌሎች ዘርፈ ብዙ ተግባራትን የከወነበት ዓመት ነበር፡፡ በዚህም ረገድ ባንኩ የውጭና የውስጥ ወቅታዊ ክስተቶችን ከግምት በማስገባት ይበልጥ ተወዳዳሪነቱንና ለደንበኛ ተደራሽነቱን በሚያሳድግና የባለአክስዮኖቹን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ ስትራቴጂክ ዕቅዱን ክለሳ በማድረግ ወደ ስራ ገብቷል፡፡ ባንኩ ለረጅም ዓመታት ሲጠቀምበት የነበረውን የኮር ባንኪንግ ሲስተም ወደተሻለና የቅርብ ጊዜ ስሪት ወደ ሆነው T24 version 2020 የማሳደግ ስራውን አጠናቀቆ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል፡፡ ይህም የባንኩን ዋና ዋና የሥራ ሂደቶች በማቀላጠፍ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ምቹ ሁኔታን ከመፍጠሩም ባሻገር ከሲስተም መቆራረጥ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን የደንበኞችን ቅሬታ ቀርፏል፡፡

በበጀት ዓመቱ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የዳታ ሴንተር ለማደራጀት፣ ለመገንባትና ለመተግበር የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በተጨማሪም ሁሉንም ወሳኝ የሥራ ሂደቶች የሚያሳልጥ አዲስ የኮምፒዉተር መሰረተ ልማት ግንባታ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡

ባንኩ በሌላ በኩልም የዘመኑ ቴክኖሎጂ በባንክ ኢንዲስትሪው ዘርፍ ያመጣውን ለውጥ ያገናዘበ የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ቀርጾ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ ከነዚህ ውስጥም ኢ-ብር ከሚባል ኩባንያ ጋር በተመተባበር “NIB E-Birr” የሞባይል ዋሌትና የኤጀንሲ ባንኪንግ አገልግሎቶችን በማቅረብ የባንኩን የዲጅታል ክፍያ መንገዶችን ከተለያዩ የሶስተኛ ወገን የክፍያ ስርዓቶች ጋር ትስስር በመፍጠር ደንበኞች የተለያዩ ሂሳቦችን ለመክፈል ምቹ ሁኔታ የተፈጠረላቸው ሲሆን ለአብነትም የአየር ትኬት ለመቁረጥ፣ የሞባይል አየር ሰዓት ለመግዛት፣ የትምህርት ቤት ክፍያ፣ የትራፊክ ቅጣት፣ ታክስ ክፍያ እንዲሁም ገንዘብ ከአንድ ባንክ ወደሌላ ባንክ በሞባይል ማስተላለፍ እንዲችሉ ተደርጓል፡፡

ከዚህም ባሻገር ባንኩ የደንበኞች አገልግሎት ጥሪ ማዕከል አቋቁሞ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት በማድረግ ከተለያዩ ድርጅቶች ለአብነትም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከኢትዮ-ቴሌኮም፣ ከኢ-ብር ኩባንያ፣ ከቀላል ትራንስፖርት፣ ከበርካታ ትምህርት ቤቶች ወዘተ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ስምምነቶችን ተፈራርሞ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

ባንኩ በበጀት አመቱ ለመዲናችን አዲስ አበባ ተጨማሪ ውበትንና ግርማ ሞገስን ያጐናፀፈውን በዓይነቱ ልዩና ዘመናዊ ባለ 37 ወለል የዋና መስሪያ ቤት ሕንፃ አስመርቆ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ከማስገባቱም ባሻገር በሃዋሳ ከተማ ውስጥ እያስገነባ ያለው ባለ 9 እና 11 ወለል መንታ ሕንፃም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ ከነዚሀም ባሻገር ባንኩ በወልቂጤ፣ በዱከም፣ በሆሳእና እንዲሁም በአዲስ አበባ አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል አጠገብ ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁ ህንፃዎች ሲኖሩት በዚህም ባንኩ የባለአክስዮኖቹን ሃብት ዘላቂነት ባለው ሃብት የማፍራት ሂደት ላይ አጠናክሮ ማዋሉን ያመለክታል፡፡

በበጀት አመቱ ደንበኞች ባሉበት አካባቢ ለመድረስ እና አዳዲስ ደንበኞችን ለማፍራት በተደረገው የቅርንጫፍ ማስፋፋት ስራ 29 ተጨማሪ ቅርንጫፎች ተከፍተዋል፡፡ ይህም በበጀት አመቱ ማብቂያ የባንኩን አጠቃላይ የቅርንጫፍ ብዛት 41ዐ አድርሶታል፡፡

ከዛሬ 23 ዓመት በፊት የተመሠረተው አንጋፋው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ እ.ኤ.አ. በሰኔ 3ዐ ቀን 2ዐ22 አጠቃላይ የባንኩ ሠራተኞች ብዛት 7578 መድረሱም ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያረጋግጣል፡፡

ይሠሯል ከልብ እንደ ንብ!

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ

NIB BANK

NIB BANK

Committed To Services Excellence

Share this post with

Recent Posts

News

ባንካችን ያጋጠመውን ጊዜያዊ ችግር በአጭር ጊዜ ለመፍታት ከደንበኞች፣ ከሠራተኞችና ከባንኩ

Read More

You May Also like

Reports

Jobs