ባንኩ የ2025/26 በጀት ዓመት አመታዊ የማኔጅመንት ሥራ አፈጻጸም ግመገማ መርሐ ግብሩን ሐምሌ 17 እና 18/2018 ዓ.ም የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ ከፍተኛ የማኔጅመንት አመራሮች፣ የዲስትሪክት ዳይሬክተሮች እንዲሁም የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች በተገኙበት በባንኩ ዋና መ/ቤት የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ አካሄዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሺሰማ ሸዋነካ፣ ባንኩ የበጀት ዓመቱን በተሻለና አመሪቂ በሆነ አፈጻጸም ማጠናቀቁን ገልጸው ለዚህም የባንኩን ማኔጅመንት፣ መላው ሠራተኛውን እንዲሁም ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል፡፡ በያዝነው የ2026/27 አዲስ በጀት ዓመትም በሁሉም መስኮች በርካታ ሥራዎች የሚጠበቁ መሆኑን ጠቁመው የዲጂታል አገልግሎትን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግና ደንበኛ ተኮር ሥራዎች በመሥራት የላቁ ስኬቶች የምናስመዘግብበት ይሆናል ብለዋል፡፡
የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሄኖክ ከበደ በበኩላቸው ባንካችን በታለመው የሶስት አመት ስትራቴጂ እቅድ መሰረት ዋና ዋና በሚባሉ መለኪያዎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን አመልክተዋል፡፡ በተለይ በያዝነው በጀት ዓመት በዲጂታል የባንክ አገልግሎት፣ በተቀማጭ ገንዘብና በሀብት አሰባሰብ ዘርፎች፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝት የተሻሉ ሥራዎችን በመሥራት የላቁ ስኬቶች የምናስመዘግብበትና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ በማድረግ ባንኩን ወደ ላቀ ከፍታ የምናደርስበት ይሆናል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም በአፈጻጸማቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ዲስትሪክቶች፣ ቅርንጫፎች እና መምሪያዎች ምስጋናና ዕውቅና የመስጠት ሥነ ስርዓት ተካሄዶ ተጠናቋል፡፡





