ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር፣ ለደንበኞቻቸው የላቀ ተጠቃሚነት ለመፍጠር እና የጋራ የሥራ እድሎችን ለማስፋፋት ያለመ ውይይት ዛሬ ሐምሌ 22 ቀን 2018 ዓ.ም አካሄደዋል።
በውይይት መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሄኖክ ከበደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሀገራችን የኩራት ምንጭ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ስም በክብር የሚያስጠራ ግንባር ቀደም ተቋም መሆኑን ጠቅሰው፣ ቢሾፍቱ እየተገነባ በሚገኘው ዘመናዊ የአየር መንገድ ባንኩ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። በሌላም በኩል ባንኩ ዘመናዊ፣ አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ “ንብተራ ኦንላይን” የተሰኘ የዲጂታል ባንክ መተግበሪያ ያለው መሆኑን በመግለጽ፣ ደንበኞች ከየትኛውም ቦታና በማንኛውም ጊዜ የፋይናንስ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ 80ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን እያከበረ ባለበት በዚህ ወቅት ይህ ውይይት መካሄዱ ልዩ ትርጉም እንዳለው የገልፁት አቶ ሄኖክ፣ ለአየር መንገዱ አመራሮችና ለመላው ሠራተኞቹ “እንኳን ለ80ኛ ዓመት የምሥረታ በዓላችሁ አደረሳችሁ!” በማለት ከልብ የመነጨ ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፣ አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ባንዲራ በኩራት የሚያውለበልብ ግንባር ቀደም ተቋም መሆኑንና ለሀገራችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከሚያስገኙ ተቋማት መካከል ቀዳሚ ስፍራ እንደሚይዝ ገልጸዋል። አየር መንገዱ ዛሬ ላይ ያለበት ስኬት የደንበኞቹ፣ የሠራተኞቹና የንግድ አጋሮቹ የጋራ አስተዋጽኦ ውጤት መሆኑን በመግለጽ፣ ከንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር ያሉትን የትብብር እድሎች በማስፋትና ያሉ ክፍተቶችን በመሙላት በቀጣይ ይበልጥ ተቀራርበው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በውይይቱ የባንክና የአቪዬሽን ዘርፎችን የሚያስተሳስሩ የተለያዩ የንግድ ትብብሮችን የማጠናከር፣ የዲጂታል ክፍያ ስርዓቶችን የማስፋፋት፣ ለደንበኞቻቸው ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና አስተማማኝ አገልግሎቶችን በጋራ ለማቅረብ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።
በመጨረሻም፤ ሁለቱ ተቋማት በጋራ በመስራት ለደንበኞቻቸው የላቀ እሴት እንደሚፈጥር፣ የሥራ ትብብራቸውን በቀጣይነት እንደሚያጠናክር እና ለሀገራችን ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የበለጠ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አረጋግጠዋል።
***
ይሠሯል ከልብ፣ እንደ ንብ!



