ባንኩ 25ኛ አመት የምሥረታ በአሉን በተለያዩ መርሐ-ግብሮች እያከበረ ለወራት የቆየ ሲሆን የአባበሩ አካል የሆነውን “የሠራተኞች ቀን” በበጎ አድራጎት ማኅበራቱ በተለያዩ ሁነቶች አክብሯል፡፡
የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አቶ ሄኖክ ከበደ በመቄዶኒያ የአረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ባደረጉት ንግግር፤ በባንኩ የ25 አመታት ስኬታማ ጉዞ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ሠራተኞችን በማመስገን “እንኳን አደረሳችሁ፤ እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል፡፡ ባንኩ ሲመሰረት ጀምሮ እስካሁን እያገለገሉ የሚገኙ ሠራተኞችን በልዩነት ያመሰገኑት ዋና ሥራ አሥፈጻሚው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በገነባው የትጉህ ሠራተኛና ሥራ ባህል ስኬቱን ማስቀጠል መቻሉን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን ባለውለታ የሆነው መቄዶኒያ የበጎ አድራጎት ማዕከል ለዘመናት በእቅፉ ያስጠለላቸው ወገኖች የሁሉም ዜጋ የማያቋርጥ ድጋፍ የሚሹ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ሄኖክ፤ “የዛሬውን ልዩ የሠራተኞች ቀን በዚህ ውድ ተቋም ከአረጋውያን ጋር ስናከብር ወሰን በሌለው ፍቅርና ክብር ጭምር መሆኑንም ከልብ ልገልጽ እወዳለሁ” ብለዋል፡፡ በዚህም ባንኩ በቻለው አቅም ለማዕከሉ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመጠቆም የማዕከሉ መሥራችና ሥራ አሥኪያጅ የክብር ዶክተር ቢንያም በለጠን በእጅጉ አመስግነዋል፡፡
የመቄዶኒያ የአረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል መሥራችና ዋና ሥራ አሥኪያጅ የክብር ዶክተር ቢንያም በለጠ በበኩላቸው የንብ ኢንተርናሽናል ባንክን በመላው የማዕከሉ ተጧሪዎች ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
“አብዛኞቹ ተቋማት እንዲህ አይነት ፕሮግራሞቻቸውን የት እንደሚያሳልፉ የሚታወቅ ነው” ያሉት ዋና ሥራ አሥኪያጁ “ንብ ባንክ በ25ኛ አመት የምሥረታ በዓሉ የሠራተኞች ቀንን በዚህ ማዕከል ከአረጋውያንና አቅመ ደካሞች ጋር ለማሳለፍ በመወሰኑ እጅግ ኮርተናል፡፡ ፈጣሪ የሚወደውንም ተግባር ፈጽማችኋል” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ባንኩ የሠራተኞች ቀን በዓሉን ባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ማኅበር በተመሳሳይ መርሐ-ግብር አክብሯል፡፡
የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የኢንተርናሽናል ባንኪንግ ምክትል ቺፍ ኦፊሰር ወ/ሮ ሐረገወይን አምሳለ ባደረጉት ንግግር ለሰራተኞች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን “የሰራተኞች ቀን ከተለመደው ለየት ባለ መንገድ በባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ማኅበር በማክበራችን ልዩ ደስታ ፈጥሮልናል” ብለዋል፡፡ ባንኩ ከዚህ ቀደም በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ሲደግፍ መቆየቱን ጠቅሰው ወደፊትም እንደ ባቡል ኸይር የመሳሰሉ ድርጅቶችን በመደገፍ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የሸሪዓ አማካሪ ሰብሳቢ ሸይኽ አብራር ሺፋ በበኩላቸው የሰው ደሰታ ለሰዎች መትረፍ ነው፣ የሃይማኖትም የሰውነትም መለኪያ ሰውን ማገዝ ነውና በሰብዓዊነት ላይ መበረታት እንዳለበት አጽዕኖት ሰጥተዋል።
የባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ማኅበር መስራችና ተወካይ ወ/ሮ ፈትያ መሐሙድ ባደረጉት ንግግር ባንኩ የሠራተኞች ቀንን እንዲህ ባለው መልኩ ማክበሩ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡
በመርሐ-ግብሩ የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀ-መንበር አቶ ሺሰማ ሸዋነካን ጨምሮ የቦርድና የማኔጅመንት አባላት ሁለቱንም ማዕከላት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡ አረጋውያንን የመመገብ ሥራም አከናውዋል፡፡