የንብ ኢንተርናሽናል  ባንክ ስትራተጂክ ዕቅድ ዝግጅት የውል ስምምነት  

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚገለገልበትን ስትራተጂካዊ ዕቅድ ለማዘጋጀት አሸናፊ ከሆነው ኬፒኤምጂ ኢስት አፍሪካ ሊሚትድ ከተባለ ኩባንያ ጋር መጋቢት 26 ቀን 2010 ዓ.ም የውል ስምምነት ፊርማ ሥነ ሥርዓት ተካሄደ፡፡

የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት በሚገኝበት ቦሌ መንገድ ደምበል ሲቲ ሴንተር የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ፣ ሥራ አስፈጻሚዎችና የኬፒኤምጂ ተወካዮች በተገኙበት፤ ባንኩን በመወከል የባንኩ ፕሬዚደንት አቶ ክብሩ ፎንጃ፣ ኬፒኤምጂ ኢስት አፍሪካ ሊሚትድን በመወከል ደግሞ የኩባንያው ዳይሬክተር ሚ/ር ዴቪድ ሌሂ የፊርማውን ሥነ ሥርዓት አከናውነዋል፡፡

የጨረታ ሰነዱን ከወሰዱት 23 ድርጅቶች መካከል ስምንት አገር አቀፍና የውጭ ድርጅቶች የጨረታ ሰነዳቸውን አስገብተው በተደረገው ቴክኒካዊ ምዘናና ማጣራት፣ ኬፒኤምጂ ኢስት አፍሪካ ሊሚትድ የተሻለ ውጤት በማግኘት ጨረታውን ለማሸነፍ ችሏል፡፡    

ስትራተጂካዊ ዕቅዱ የባንኩን ድርጅታዊ አወቃቀር ከዘመኑ ጋር እንዲዘምን በማድረግ ለተገልጋዩም ሆነ ለሠራተኛው የተሻለ ዕድል ለመፍጠር ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአሁኑ ወቅት የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 25 ቢሊዮን፣ ተቀማጭ 20 ቢሊዮን፣ ብድር 13 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን፤ 209 ቅርንጫፎችና ከ4 ሺህ በላይ ሠራተኞችን የሚያስተዳድር በአገሪቱ ከሚገኙ ግንባር ቀደም የግል ባንኮች አንዱ ነው፡፡