የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ 18ኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄደ

የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የባለአክሲዮኖች 18ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ህዳር 9 ቀን 2010 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በተሳካ ሁኔታ ተካሂዷል፡፡ ጉባኤው በበጀት አመቱ የተገኙ ውጤቶችን በሥራ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችና በቀጣይ የሥራ ዘመን የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ  ውይይት አድርጓል፡፡

በተለይም ችግሮችን ለመቅረፍ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ አስፈላጊ የሆኑ ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎች እና የአሠራር ዘዴዎች   ተግባራዊ በመሆናቸውና ባንኩ የደንበኞቹን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶች ሥራ ላይ እንዲውሉ መደረጉ ተገልጿል፡፡

በዚሁም መሠረት በበጀት ዓመቱ አመርቂ ውጤት ሲመዘገብ፣ የባንኩ አጠቃላይ ሀብት (Assets) ብር 21,00 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ካለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ32.8 ዕድገት አሳይቷል፡፡  በተለያዩ ንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች  ለተሰማሩ ባለሀብቶች ባንኩ የሠጠው የብድር መጠን ብር 10.9 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ይህም ካለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር  የ42.4 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፣ በሌላ በኩል የባንኩ የተቀማጭ መጠን ብር 16.4 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ካለፈው 32.1 በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ ባንኩ በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲሆን የካፒታል መጠን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን በማመን የተከፈለ ካፒታል መጠንን በ19 በመቶ በማሳደግ ብር 1.7 ቢሊዮን ጠቅላላ ካፒታልንም ብር 2.95 ቢሊዮን አድርሷል፡፡ ባንኩ በሂሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት ብር 681.5 ሚሊዮን ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን ይህም  የ48.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የተጣራ ትርፍ ከትርፍ ግብር በኋላ ደግሞ ብር 516.4 ሚሊዮን ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ159.7 ሚሊዮን ብር ወይም የ44.8 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ በዚህም የትርፍ ክፍፍል ደርሻ 31.4 በመቶ ሲሆን ይህም ከነበረው 25.8 በመቶ ጋር ሲነፃፀር በ5.8 መቶ ከፍ ብሏል፡፡

ባንኩ ደንበኞቹን በቅርበት ለማገልገልና ምቾታቸውን ለመጠበቅ የአገልግሎት አድማሱን  በመላው አገሪቱ ለማስፋት በበጀት ዓመቱ 50 ቅርንጫፎች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ላይ በመክፈት የቅርንጫፎቹን ብዛት 180 አድርሷል፤ 73 አዳዲስ የካርድ ማሽኖችን (ATM) በተለያዩ ቅርንጫፎች፣ በሆቴሎችና በተለያዩ የንግድ ማዕከሎች በመትከል ቁጥራቸውን 150 አድርሷል፣ የክፍያ መፈፀሚያ ማሽኖችን (POS Machines)፣ የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎትን አጠናክሮ በመቀጠል ደንበኞች በማንኛውም ጊዜና ቦታ  ውስጥ ሆነው አገልግሎቱን  እንዲጠቀሙ እያደረገ ይገኛል፡፡

ባንኩን ይበልጥ በማዘመን ስራዎችን ለማቅለልና የባንኩን የገንዘብና የሰው ኃይል ባግባቡ ለመጠቀም ያስቻሉ የተለያዩ ሲስተሞች (System Solutions) ተግባራዊ ሆነዋል።  አገልግሎት እየሰጠ ያለውን የT24 ኮር ባንኪንግ ሲስተም (Core Banking System) ወደተሻለ ደረጃ የማሳደግና  አዳዲስ የአገልግሎት ዓይነቶችን (Features) እንዲኖረው የማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

የባንኩ 3ኛውን የአምስት ዓመት የስትራቴጂክ ዕቅድና የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት  የታወቁ አማካሪ ድርጅቶችን በመጋበዝ የጨረታ ግምገማው እየተከናወነ ነው።

ባንኩ በጠንካራ መሠረት ላይ ለማቆም እንዲሁም አገልግሎቱን በራሱ ህንፃ ላይ ለማከናወን እንዲችል የግዥና የግንባታ ስራዎች በተሣካ ሁኔታ እየተሠሩ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሠረት የዋና መስሪያ ቤት ግንባታ በአጥጋቢ ሁኔታ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን ዱከም ከተማ ውስጥ ያስገነባው ህንፃ በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን ፣ ባለ12ቱ ወለል ሕንፃም የመሠረት ቁፋሮ ተጠናቆ የግንባታው ሥራ ተጀምሯል ከዚህም በተጨማሪ የሆሳዕና ባለ አራት ፎቅ ሕንፃ ግንባታ የማጠናቀቂያ ሥራውን ለማከናወን በጨረታ ሂደት ላይ ይገኛል።

በሌላ በኩል በህግ ተይዞ የነበረውና በመከታ ሪል ስቴት ኃላ/የተ/የግል ማህበር የተገነባው አራት ኪሎ የሚገኘውን ህንፃ ባንኩ በተካሄደው ግልፅ ጨረታ ተካፍሎ በማሸነፍ ህንፃውን ተረክቦ የማጠናቀቂያ ሥራ ለማከናወን በሂደት ላይ ይገኛል፡፡

ባለአክሲዮኖቹ በቀረቡት አጀንዳዎች ላይ በቂና ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ኣሳልፏቸዋል፡፡ በመጨረሻም ለቀጣዩ 3 ዓመታት ባንኩን በበላይነት የሚመሩትን የዲሬክተሮች ቦርድ በመምረጥ ጉባዔው ተጠናቋል፡፡